የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር፣ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በይፋ አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር፣ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በይፋ አስጀምሯል።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ መርሃ ግብሩን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፣ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ ተቋማት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለየ ጊዜ የሚጠብቁ ሳይሆን በየዕለቱ የሚያከናውኑት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በተዘጋጀው መርሃ ግብር ከ14 በላይ ትኩረት የሚሹ ተግባራት ተካትተው፣ ነፃ የምርመራና የሕክምና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ በስፋት ለማድረስ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር ሰላማዊት አክለውም፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለኩላሊት ሕሙማን የዲያሊሲስ አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ላለው ያላሰለሰ ጥረት ምስጋና አቅርበው፣ በቀጣይም በትብብር የችግረኞችን ሕይወት ለመታደግ ሁሉም አካላት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደቡብ ክላስተር አስተባባሪና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ ፣ የኩላሊት ሕመም በርካታ ወገኖችን ለህልፈት እየዳረገ ቢሆንም የዲያሊሲስ አገልግሎት በሀገር ደረጃ አሁንም በበቂ ሁኔታ ተደራሽ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ከሜሪጆይ ኢትዮጽያ ጋር በመተባበር የኩላሊት ህመምተኞችን ለመደገፍ፣ እንዲሁም የኩላሊት ህክምናን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍፁም ወልደገብርኤል በበኩላቸው፣ መርሃ ግብሩ ወደ ጤና ተቋማት መድረስ ላልቻሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በመድረስ አገልግሎት የሚሰጥበት ጠቃሚ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፣ በቅንጅት የሚከናወኑ ስራዎች ውጤታማነታቸውን እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል።
አያይዘውም፣ በእየጨመረ የመጣውን የኩላሊት ሕመም ለመቀነስ በ2019 ዓ.ም በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት
ሕክምና ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው፣ በሀዋሳ የሚገኘው የዲያሊሲስ ማዕከል በዝቅተኛ ክፍያ ቢያገለግልም የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የማህበረሰቡ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች በወር 200 ብር ብቻ በመክፈል አባል በመሆን የታካሚዎችን ሕይወት ለመታደግ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች ለSBC በሰጡት አስተያየት የበጎ አድራጎት ስራ የአንድ ወቅት ተግባር ብቻ መሆን እንደሌለበት ገልፀዋል ።
በተቋሙ የተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ነፃ የጤና ምርመራና ሕክምና፣ የደም ልገሳ መርሃ ግብሮች እና የጤና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎቶችን የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።


አስተያየትዎን ያጋሩ
ቋንቋ ይቀይሩ
ፍለጋ
ወቅታዊ ዜናዎች
የስራ ማስታወቂያ
SBC
የፌስቡክ ገጽ
ዩቲዩብ