ምክር ቤቱ የዋና ኦዲተር ሪፖርትን አፀደቀ ።

ምክር ቤቱ የዋና ኦዲተር ሪፖርትን አፀደቀ ።
ምክር ቤቱ የዋና ኦዲተር ሪፖርትን አፀደቀ ።
*************
ሀዋሳ- መስከረም 19/01/2019 ዓ.ም(ኤሲቢስ)
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ዘመን 5ኛ የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው የክልሉ ዋና ኦዲተር ሲምቦ ሽብሩ የ2018 ዓ.ም የኦዲት አፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በበጀት ዓመቱ 211 መሥሪያ ቤቶች ኦዲት መደረጋቸውን ዋና ኦዲተሩ ገልጸው፣ ኦዲት በተደረጉ አንዳንድ ተቋማት የበጀት አጠቃቀም ላይ ክፍተት እንዳልታየ አመልክተዋል።
ነገር ግን በኦዲት ግኝቶች ክፍተት የታየባቸው የሴክተር ተቋማት ላይ የምክር ቤቱ ክትትል እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
በተለይም የክዋኔ ኦዲት ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉና በከተሞች በተደረጉ ኦዲቶች የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
አላስፈላጊ የበጀት አጠቃቀሞች እንዲስተካከሉና የኦዲት ሪፖርቶች አጠቃቀም እንዲጠናከርም ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፣ ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ክልሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኦዲት ግኝቶች የታዩ ክፍተቶችን ለማረም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የኦዲት ሪፖርቱን በቀረበው ልክ በመረዳት ለለውጥ መነሳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የምክር ቤት አባላትም ብልሹ አሠራሮችን ለመታገል ቁርጠኛ በመሆን ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለባቸው ጠቁመው፣ በአሠራር ላይ ክፍተት ያሳዩ አካላት በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ግልጽ መሆኑን ገልጸው፣ በየሴክተሩ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ የኦዲት ሪፖርት ያለው ሚና እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
ሕገወጥ ተግባራትን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሕጋዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድም አሳስበዋል።
እንዲሁም በአፈጻጸም ምሳሌ የሚሆኑ ተቋማት ሊበረታቱና ሊመሰገኑ፣ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ተቋማት ደግሞ ያሉባቸውን ክፍተቶች በመገምገም ለለውጥ መነሳት እንዳለባቸው አባላቱ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የቀረበውን ሪፖርት በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል ።
ቆንጅት አየለ
ለሃሳብ ልዕልና
ቀጣዮቹን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን የኤስቢሲ ቤተሰብ ይሁኑ!

አስተያየትዎን ያጋሩ
ቋንቋ ይቀይሩ
ፍለጋ
ወቅታዊ ዜናዎች
የስራ ማስታወቂያ
SBC
የፌስቡክ ገጽ
ዩቲዩብ